በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የማዳምጠው ሙዚቃ ለውጥ ያመጣል?

የማዳምጠው ሙዚቃ ለውጥ ያመጣል?

 “ጠዋት ቀኑን የምጀምረው ሙዚቃ በማዳመጥ ነው። መኪና ውስጥ ስገባም ሙዚቃ እከፍታለሁ። ቤት ውስጥ ዘና ስል፣ ቤት ሳጸዳ ሌላው ቀርቶ ሳነብ እንኳ ሙዚቃ አዳምጣለሁ። ሙዚቃ የማልሰማበት ጊዜ የለም።”—ካርላ

 አንተም እንደ ካርላ ሙዚቃ ትወዳለህ? ከሆነ ይህ ርዕስ በምታዳምጠው ሙዚቃ እንድትደሰት፣ ከሚያስከትለው ጉዳት እንድትርቅና የምታዳምጠውን ሙዚቃ በጥበብ እንድትመርጥ ይረዳሃል።

 ጥቅሞች

 ሙዚቃ ማዳመጥ፣ ምግብ ከመብላት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የምንመገበውም ምግብም ሆነ የምናዳምጠው ሙዚቃ፣ ዓይነቱም ሆነ መጠኑ ትክክለኛ መሆኑ ጠቃሚ ነው። የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት፦

  •   ሙዚቃ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል።

     “የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመኝ የምወደውን ሙዚቃ አዳምጣለሁ። ወዲያውኑ የመረጋጋት ስሜት ይሰማኛል።”—ማርክ

  •   ሙዚቃ ያለፈውን ጊዜ ያስታውስሃል።

     “ያሳለፍኩትን ጥሩ ጊዜ የሚያስታውሱኝ ዘፈኖች አሉ፤ ዘፈኑን በሰማሁት ቁጥር ደስ ይለኛል።”—ሺላ

  •   ሙዚቃ ጠንካራ ትስስር ይፈጥራል።

     “የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ነበር፤ ሁሉም ልዑካን የመደምደሚያውን መዝሙር ሲዘምሩ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም። የተለያየ ቋንቋ ብንናገርም ሙዚቃው አንድ አድርጎናል።”—ታሚ

  •   ሙዚቃ አስፈላጊ ባሕርያትን እንድታዳብር ይረዳሃል።

     “የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት መማር ራስን መግዛትና ትዕግሥት እንድታዳብር ይረዳሃል። በአጭር ጊዜ ውስጥ የምትችለው ነገር አይደለም። ችሎታህን ልታሻሽል የምትችልበት ብቸኛው መንገድ ልምምድ ማድረግ ነው።”—አና

 ይህን ታውቅ ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ትልቁ መጽሐፍ ማለትም የመዝሙር መጽሐፍ፣ የ150 መዝሙሮች ስብስብ ነው።

የምትመገበውን ምግብ እንደምትመርጥ ሁሉ የምታዳምጠውንም ሙዚቃ መምረጥ አለብህ

 ጉዳቶች

 አንዳንድ ሙዚቃዎች ልክ እንደ ተበላሸ ምግብ መርዛማ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ የሆነበትን ምክንያት ተመልከት።

  •   በርካታ ዘፈኖች የብልግና ግጥሞችን ይዘዋል።

     “ተወዳጅ የሆኑት ዘፈኖች ሁሉ የሚናገሩት ስለ ፆታ ግንኙነት ብቻ ይመስላል። አሁን አሁን ለመሸፋፈን እንኳ አይሞክሩም።”—ሐና

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የፆታ ብልግናና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ።” (ኤፌሶን 5:3) ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘የማዳምጠው ሙዚቃ ይህን ምክር ተግባራዊ እንዳላደርግ እንቅፋት ይሆንብኛል?’

  •   አንዳንድ ሙዚቃዎች በሐዘን እንድትዋጥ ሊያደርጉህ ይችላሉ።

     “አንዳንድ ጊዜ ምሽት ላይ አልጋዬ ውስጥ ሆኜ፣ በሐዘን እንድዋጥና እንድጨነቅ የሚያደርግ ሙዚቃ አዳምጣለሁ። የሚያሳዝን ሙዚቃ አሳዛኝ ነገሮች ወደ አእምሮዬ እንዲመጡ ያደርጋል።”—ታሚ

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ከምንም ነገር በላይ ልብህን ጠብቅ።” (ምሳሌ 4:23) ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘የማዳምጠው ሙዚቃ አፍራሽ በሆኑ ሐሳቦች ላይ እንዳተኩር ያደርገኛል?’

  •   አንዳንዱ ሙዚቃ ቁጡ ሊያደርግህ ይችላል።

     “ቁጡ እንድንሆን ወይም ለራስም ሆነ ለሌሎች ጥላቻን እንድናዳብር የሚያደርጉ ሙዚቃዎች ስውር ወጥመድ ሆነውብኝ ነበር። እንዲህ ያለ ሙዚቃ ማዳመጥ በስሜቴ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ አስተውያለሁ። ቤተሰቦቼም ይህን ለውጥ ማስተዋል ችለዋል።”—ጆን

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ቁጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትንና ስድብን ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ፤ ጸያፍ ንግግርም ከአፋችሁ አይውጣ።” (ቆላስይስ 3:8) ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘የማዳምጠው ሙዚቃ፣ ብስጩ ምናልባትም ለሌሎች ስሜት ግድ የለሽ እንድሆን ያደርገኛል?’

 ዋናው ነጥብ፦ መራጭ ሁን። ጁሊ የተባለች ወጣትም ያደረገችው ይህንኑ ነው። እንዲህ ብላለች፦ “ያሉኝን ሙዚቃዎች በየጊዜው የምመረምር ሲሆን ተገቢ እንዳልሆኑ የተሰሙኝን ሙዚቃዎች በሙሉ አጠፋለሁ። እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም፤ ሆኖም ማድረግ ያለብኝ ነገር እንደሆነ አውቃለሁ።”

 ታራ የተባለች ወጣትም ተመሳሳይ ነገር አድርጋለች። እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ሬዲዮ ላይ ደስ የሚል ምት ያለው ሙዚቃ ያጋጥመኛል፤ ግጥሙን ስሰማ ግን ጣቢያውን መቀየር እንደሚኖርብኝ እገነዘባለሁ። ይህን ማድረግ ግን በጣም የሚጣፍጥ ኬክ አንድ ጊዜ ብቻ ቀምሶ ለማቆም ራስን እንደማስገደድ ከባድ ነው! ቢሆንም ስለ ፆታ ግንኙነት የሚናገር ግጥም ያለውን ዘፈን የምቃወምበት ጥንካሬ ካለኝ፣ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸምን የምቃወምበት ጥንካሬ ይኖረኛል። የማዳምጠው ሙዚቃ በእኔ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አቅልዬ መመልከት አልፈልግም።”